በኮንሶ ዞን የKIA ሀገር በቀል ሲቪክ ማህበር ከኮንሶ ዞን አስተዳደር ጽፈት ቤት ጋር በመተባበር ለአመራሩ ለተከታታይ ሁለት ቀናት ሲሰጥ የቆየው የአመራር ስልጠና ተጠናቀቀ።
አመራሩ በመተባበር፣ በመቀናጀት፣ በዕውቀትና በጥበብ ህዝብን ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውንም አመራሩ አስታውቋል።
የኮንሶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጅነር ፍሬዘር ኮርባይዶ የኮንሶ ምሁራን ማህበርን አመስግነው፤ ስልጠናውን የተካፈለ አመራር ሁሉ ስልጠናውን ወደ ተግባር በመቀየር ህዝባችንን በዕውቀት ለውጤት ማገልገል አለበት ብለዋል።









የኮንሶ ምሁራን ማህበር ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ ር አማኑኤ ኩሲያ ቃል የገባነውን በመተግበር ህዝባችንን ማገልገል ያስፈልጋል ብለዋል።
ዶ/ር አማኑኤል አክለውም አገልጋይ ተቋማትን መፍጠርና ለውጥ በዕውቀት መስራት እንደሚገባና የለውጥ መሪ መሆን እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።
ስልጠናው በቀጣይ ለወጣቶች፣ ለሴቶች ብሎም ለሲቪል ሰርቫንቱ እና ለነጋደው ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰሩ ዶ/ር አማኑ ጠቁመዋል።
የኮንሶ ምሁራን ማህበር ዋና ጸሐፊ ዕጩ ዶክተር አስቻለው ኮራ በበኩላቸው የመሰረተ ልማትና የተለያዩ ችግሮችን ለመፍታት በትብብር እና በአንድነት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
የኮንሶ ምሁራን ማህበር ሰብሳቢ አቶ ኩማቸው ኩሴ በስልጠናው ራሳችንን ማየት የምችልበት እንዲሁም ለመማማር የተዘጋጀንበት መድረክ በመሆኑ ሁላችንም የተናገርነውን ልንኖር ይገባል ብለዋል።
የማህበሩ ሰብሳቢ አቶ ኩማቸው፤ አክለውም KIA ሀገር በቀል ሲቪክ ማህበሩ በቀጣይ የተሻለ ስራ የሰሩ አካላትን እውቅና የሚሰጥበት ሂደት እንደሚኖር ጠቁመዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች ስለስልጠናው አስተያየታቸውን የሰጡ ሲሆን፤ የነበርንበትን ሁኔታ በአግባቡ ያስቃኘን እና በርካታ እዉቀቶችን ያገኘንበት ስልጠና በመሆኑ እጅግ ተደስተናል ብለዋል።
ከስልጠናው ያገኘነውን ክህሎት ከወሬና ከአሉባልታ በመራቅ በተግባር መግለጥ ይኖርብናል ለዚህም ዝግጁ ልንሆን ይገባል ብለዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ረዳት የመንግስት ተጠሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ በማጠቃለያው ስልጠናው አስደሳች እና ብዙ ውጤት የሚጠበቅበት መሆኑን ገልጸዋል።
አመራሩ ከከፋፋይ አጀንዳ በመራቅና የመንግስት እና የማህበሩን የስራ ሀላፊነቶችን ለይቶ መስራት፣ ጥርጣሬና መናቆርን በማጥፋት፣ ለኮንሶ ለውጥና እድገት በጋራ መቆም ያስፈልጋል ብለዋል።
በስልጠናው የኮንሶ ብሔረሰብ ተወካይና ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ የተከበሩ አቶ ሰለሞን ሶካ፣ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ፍሬዘር ኮርባይዶ፣ የዞኑ ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ ሐመር ሐንሻን ጨምሮ የኮንሶ ምሁራን ማህበር አመራሮች፣ ከሁሉም ወረዳና ከተማ አስተዳደር የመጡ ከፍተኛና መካከለኛ አመራርን ያሳተፈ ስልጠናው አጠናቀዋል።
መረጃው
የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉ/መምሪያ
ሐምሌ 27/2016 ዓ.ም







