ደረሰኝ ይስጡ፣ ይቀበሉ” ዞናዊ የንቅናቄ መድረክ

የኮንሶ ዞን ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ካሳሁን ገረመው “ደረሰኝ ይስጡ፣ ይቀበሉ” ዞናዊ የንቅናቄ መድረክ ላይ ያስተላለፉት መልዕክት

ካራት፣ መስከረም 8/2018 ዓ.ም. (ኮንሶ ዞን ኮሙኒኬሽን)

እንኳን ለዚህ “ደረሰኝ ይስጡ፣ ይቀበሉ” ለሚለው ዞናዊ የንቅናቄ መድረክ በሰላም አደረሳችሁ፣ ዛሬ በዚህ መድረክ ላይ የተሰበሰብነው በዞናችን ዘላቂ ልማትና እድገት ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ያለውንና ትልቅ ትኩረት የሚሻውን የግብር ባህል ግንባታ ጉዳይ ለመምከር ነው።

እንደምናውቀው፣ ማንኛውም ህዝብና መንግስት የሚፈልገውን መሠረተ ልማት፣ የትምህርት፣ የጤናና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶችን ለማሟላት ጠንካራ የገቢ መሠረትና በራስ አቅም መቆም ያስፈልጋል ፣ይህ ደግሞ እያንዳንዱ ዜጋና ነጋዴ የሚጠበቅበትን ህጋዊ ግዴታ በታማኝነት ሲወጣ ነው እውን የሚሆነው።

የደረሰኝ ይስጡ፣ ይቀበሉ ንቅናቄ ዓላማም ቀላልና ግልጽ ነው፣ ማንኛውም ህጋዊ ነጋዴ ለሸጠው ዕቃ ወይም ለሰጠው አገልግሎት ተገቢውን ደረሰኝ የመስጠት ግዴታ አለበት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ማንኛውም ሸማች ወይም ደንበኛ ለገዛው ዕቃ ወይም ላገኘው አገልግሎት ደረሰኝ የመጠየቅና የመቀበል መብትና ህዝባዊ ኃላፊነት አለበት።

ደረሰኝ መስጠትና መቀበል ለምን አስፈለገ ከተባለ ፣ህጋዊና ፍትሃዊ የንግድ ውድድርን ያጠናክራል ፣ደረሰኝ የማይቆርጡ ነጋዴዎች ግብይታቸውን በአግባቡ ባለመመዝገብ የታክስ ግዴታቸውን ለመሰወር እድል ይፈጥራሉ፤ ይህም ህጋዊ ግዴታቸውን በሚወጡ ነጋዴዎች ላይ የውድድር መዛባት እንዲፈጠር ያደርጋል።

ሁለተኛ፣ የመንግስት ገቢ በአግባቡ እንዲሰበሰብ ያግዛል። ግብይቶች በትክክል ሲመዘገቡ የገቢ አሰባሰብ ሥርዓቱ ግልጽና የተሻለ ቁጥጥር ያለው ይሆናል ፣ የሚሰበሰበው የህዝብ ገቢም መንገድ፣ ውሃ፣ ትምህርት፣ ጤናና ሌሎች የህዝብ አገልግሎቶችንና የልማት ሥራዎችን ለመደገፍ የሚያገለግል የህዝብ ፋይናንስ መሠረት ነው።

ሶስተኛ፣ ደረሰኝ የሸማቹን መብት ይጠብቃል ፣ ሸማቹ የገዛውን ዕቃ ወይም ያገኘውን አገልግሎትና የከፈለውን ዋጋ የሚያረጋግጥ የግብይት ማረጋገጫ ያገኛል፣ ይህም የግብይቱን ግልጽነት ለማስጠበቅ ያግዛል።

በኮንሶ ዞን በህጋዊነት እየሰሩና ለዞኑ ኢኮኖሚ እድገት አስተዋጽኦ እያደረጉ ያሉ በርካታ ታማኝ ነጋዴዎች አሉ ፣ ለእነዚህ ነጋዴዎች ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና እናቀርባለን።

ሆኖም ግን፣ አሁንም ደረሰኝ ባለመቁረጥ፣ በታክስ ስወራ፣ በኮንትሮባንድና በህገ-ወጥ ንግድ የሚሳተፉ አካላት ካሉ ይህ የህጋዊ ንግድ ሥርዓታችንን፣ የፍትሃዊ ውድድርን እና የዞናችንን የገቢ አቅም ይጎዳል።

ይህንን ክፍተት በዘላቂነት ለመቅረፍ የህግ ማስፈጸም ብቻ በቂ አይደለም። የግብር ባህላችንን ማሳደግ፣ የነጋዴውንና የሸማቹን ግንዛቤ ማሳደግና በጋራ መስራት ያስፈልገናል።

ስለሆነም ለንግዱ ማህበረሰብ ጥሪዬ፣ የንግድ ሥራችሁን በታማኝነትና በህጋዊነት በማካሄድ፣ ለምታከናውኑት ማንኛውም ህጋዊ ግብይት ተገቢውን ደረሰኝ ያለምንም ማቅማማት እንድትሰጡ ነው፣ ይህን በማድረግ ህጋዊ ግዴታችሁን ከመወጣት ባለፈ ለፍትሃዊ የንግድ ሥርዓትና ለዞናችን ኢኮኖሚ እድገት አስተዋጽኦ ታደርጋላችሁ።

ለሸማቹ ማህበረሰብም ጥሪዬ፣ የምትገዙትን ዕቃ ወይም የምታገኙትን አገልግሎት ያለ ደረሰኝ እንዳትቀበሉ፤ ደረሰኝ መጠየቅና መቀበልን የዕለት ተዕለት የግብይት ባህላችሁ እንድታደርጉ ነው።

ለአመራሩና ለባለድርሻ አካላትም ይህ ንቅናቄ የአንድ ወቅት ዘመቻ ብቻ ሳይሆን ቀጣይነት ያለው የአሰራርና የግብር ባህል ለውጥ እንዲሆን በየደረጃው ክትትል፣ ቁጥጥርና ድጋፍ እንድታደርጉ ጥሪ አቀርባለሁ።

መምሪያችንም ደረሰኝ ከመስጠትና ከመቀበል ጋር የተያያዙ ህገ-ወጥ አሰራሮችን በህግ ማዕቀፍ ለመከታተልና ለማስፈጸም የሚያደርገውን ሥራ ያጠናክራል።

በመጨረሻም፣ ደረሰኝ መስጠትም ሆነ መቀበል የዜግነት ክብርና ግዴታ ነው ፣ ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን ህጋዊ ግብይትን፣ የገቢ ባህልንና የፍትሃዊ ንግድ ሥርዓትን በማጠናከር ለኮንሶ ዞን ሁለንተናዊ ልማት የየበኩላችንን እንወጣ።

ደረሰኝ ይስጡ! ይቀበሉ!

አመሰግናለሁ።
አቶ ካሳሁን ገረመው
የኮንሶ ዞን ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ

  • Giya Gina

    IS Ethiopian computer engineering graduate, journalist, and photographer who creates content focused on informing and inspiring local audiences. You can explore a portfolio of technical skills and projects on the Website. https://giyagina.22web.org

    Related Posts

    በHEKS-EPER ዓለም አቀፍ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ሚስተር ዋልተር ሽሚድ የተመራ ልዑክ ቡድን ኮንሶ ዞን ገባ

    በHEKS-EPER ዓለም አቀፍ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ሚስተር ዋልተር ሽሚድ የተመራ ልዑክ ቡድን ኮንሶ ዞን ገባ ካራት፦ ሕዳር 3/2019 ዓ.ም (ኮንሶ ዞን ኮሙኒኬሽን) በHEKS-EPER ዓለም አቀፍ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ሚስተር ዋልተር…

    ኮሙኒኬሽን ለላቀ ውጤት

    የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች “ኮሙኒኬሽን ለላቀ ውጤት” በሚል መሪ ቃል በ100 ቀናት ዕቅድና በቀጣይ ተግባራት ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በወላይታ ሶዶ ከተማ አካሂዷል። በመድረኩ የ100 ቀናት ዕቅድ እና…

    Leave a Reply

    Your email address will not be published. Required fields are marked *