የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች “ኮሙኒኬሽን ለላቀ ውጤት” በሚል መሪ ቃል በ100 ቀናት ዕቅድና በቀጣይ ተግባራት ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በወላይታ ሶዶ ከተማ አካሂዷል።

በመድረኩ የ100 ቀናት ዕቅድ እና ቀጣይ ስራ በላቀ ውጤት ከማከናወን ባሻገር የክልሉን ጸጋ አውጥቶ ለማሳወቅ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ተገልጿል።
የሚዲያ ሞኒተሪንግ ባለሙያዎች የሕዝብን አስተያየትና የሚዲያ ይዘቶችን በስልታዊ መንገድ የመከታተል፣ የመተንተንና ለተቋሙ ውሳኔ አሰጣጥ ጠቃሚ መረጃ የማቅረብ ሥራዎችን ማጠናከር እንደሚገባቸውም ተጠቅሷል።
የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ እንደገለጹት የ100 ቀናት ዕቅድ ተግባራትን ከሕዝብ ተጠቃሚነት አንጻር በመመልከት፣ አስቸኳይና ወሳኝ የሆኑ ጉዳዮችን ከተቋሙ የሥራ ኃላፊነት ጋር በማጣጣም መፈጸም እንደሚገባ አመላክተዋል።
በተለይ የሕብረተሰቡን ቅሬታ ሊፈቱና የሕዝብን ተጠቃሚነት ሊያረጋግጡ በሚችሉ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባም አቶ ኃይለማርያም ገልጸዋል።
ከዚህም ባሻገር በተቋሙ ውስጥ የሚገኙ ችግሮችን ለይቶ በመፍታት የሥራ አፈጻጸምን ማሻሻል የሚያስችሉ ተግባራትን ማከናወን እንደሚገባም አሳስበዋል።
የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ምክትል ኃላፊና የመረጃ አቅርቦት፣ ኮሙኒኬሽንና ሚዲያ ልማት ጉዳዮች ዘርፍ ኃላፊ ተሻለ ተገኔ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ሁሉም የኮሙኒኬሽን ባለድርሻ አካላት ኮሙኒኬሽንን ለላቀ ውጤት ለማድረስ የሚያስችሉ ተግባራትን በትጋት ማከናወን እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የሕዝብ ግንኙነት ሥራ መረጃን ከአንድ አካል ወደ ሌላ ማስተላለፍ ብቻ አይደለም ያሉት ዶክተር ተሻለ የመንግሥትን ዕቅዶችና ተግባራት ለሕዝብ በተገቢው መንገድ ማሳወቅ፣ አፈጻጸማቸውን መከታተልና የሕዝብን ድምፅ በማዳመጥ ግብረ መልስን የሚያካትት ሰፊ ኃላፊነት መሆኑን ገልጸዋል።
የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች የዴሞክራሲ ግንባታንና የሕብረተሰቡን በጋራ የማደግ ሂደት የሚያግዝ ሚና መወጣት እንደሚገባቸውም ምክትል ኃላፊው አሳስበዋል።
አገልግሎቱ የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎችን ሙያዊ አቅም ለማሳደግና ለተግባሩ የተሻለ ብቃት እንዲኖራቸው በቀጣይ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን እንደሚያከናውንም ጠቁመዋል።
ኮሙኒኬሽንን ለላቀ ውጤት በማዋል ጠንካራ መንግሥት የመገንባት ኃላፊነትን መወጣትና በመደመር መንግሥት ትኩረት የተሰጠውን የ100 ቀናት ዕቅድ ለማሳካት የሚያስችል የተደራጀ፣ ትክክለኛና እውነተኛ መረጃ ማዘጋጀት ከኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች የሚጠበቅ ቁልፍ ኃላፊነት መሆኑን የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ማሩፋ መኩሪያ አብራርተዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በክልሉ የሚገኙ ሚዲያዎች የክልሉን ሀብት፣ የልማት እንቅስቃሴና የሰላም ሁኔታ እንዲሁም እምቅ አቅምና የዴሞክራሲ ቁመና ለሕዝብና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በስፋት ማስተዋወቅ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።
በተጨማሪም የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት እነዚህን አጠቃላይ እንቅስቃሴዎች በተቀናጀና በተናበበ መንገድ ማስተዋወቅ የሚያስችል የአቅም ግንባታ ሥራ ማከናወን እንደሚገባም አስተያየት ሰጥተዋል።
አገልግሎቱ አሁን ላይ በተሻለ ቁመና ላይ እንደሚገኝ የጠቆሙት ተሳታፊዎቹ፣ ይህንን ለማስቀጠልና የተቋሙን አቅም ይበልጥ ለማጠናከር የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችንና የልምድ ልውውጦችን ማጠናከር እንደሚገባም አሳስበዋል።
በተለይም አጀንዳ በመቅረጽ ረገድ ቀድሞ በመገኘት፣ አዳዲስ ሥራዎችን በንቃት በማከናወን፣ የልዩ ልዩ ሚዲያ አማራጮችን በአግባቡ መጠቀምና ክልሉን የሚያስተዋውቁ ተግባራትን በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
መድረኩ ከዞን፣ ሪጂኦፖሊስ እንዲሁም ሴክተር መስሪያቤቶች ጋር በ100 ቀናት ዕቅድና ቀጣይ ተግባራት ላይ የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም ተጠናቋል። seeMore






