አመራራችን ችግሮችን ወይም ፈተናዎችን ወደ ምቹ አጋጣሚ በመቀየሮ ለለውጥ የሚሰለፍ መሆን አለበት:- ኮሚሽነር ሐልገዮ ጅሎ

በኮንሶ ዞን ያሉ አጠቃላይ አመራሮች በወቅታዊው ዓለም አቀፋዊ እና ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ መከሩ፣
”የአሜሪካ-እስራኤል እና የኢራን ጦርነት፤ ስትራቴጂካዊ አንድምታዎች እና መሻገሪያ አቅጣጫዎች!” በሚል የልሳነ ብልጽግና እሳቤ መነሻነት ምክክር ያደረጉት አመራሮቹ፤ እንደ ዓለም እና እንደ ኢትዮጵያ አሁን ላይ ያሉ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ የተሰነደ መረጃን በንባብ አድምጠዋል።
በሰነዱ ላይ ሃሳብ አስተያየታቸውን የሰጡ የምክክሩ ተካፋይ አመራሮች መጽሔቱ ወቅታዊ ጉዳይን የዳሰሰና አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮችን ያነሳ ነው ሲሉ ገልጸው፤ በሰነዱ የተዳሰሱ በርካታ ጉዳዮች አብዛኛዎቹ የእኛን አካባቢ የሚገልጹ ከመሆናቸውም በላይ በአካባቢያችን ከፍተኛ የሆነ ተጽዕኖ አሳድረዋል ብለዋል።
ከነዳጅ አቅርቦት ማነስ ጋር በማገናኘት ከአቅርቦቱ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት በሌላቸው በተለያዩ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ምክንያታዊ ያልሆኑ የዋጋ ጭማሪዎች እየተስተዋሉ በመሆናቸው የሚመለከታቸው አካላት ጉዳዩን ተከታትለው እንደዚያ በሚያደርጉ አካላት ላይ እርምጃ መውሰድ አለባቸው ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ፤ ከዚህ በኋላ ነዳጅ በሚገኝበት ጊዜ የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም ችግሮች በሚገጥሙ ሰዓት መቋቋም የሚቻልበትን ስራ መስራት ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።
ቅድመ ጥንቃቄዎችን በማድረግና የአማራጭ መንገዶችን በመጠቀም በተለየ ቅንጅት ይህንን ጊዜ ማለፍ ይገባናል፤ የውስጥ አንድነታችንን በማጠናከርና ከመናገር በዘለለ በተግባር በመገኘት የአካባቢያችንን እሴቶች ማጉላት ይጠበቅብናልም ብለዋል አመራሮቹ።
የዞኑ ረዳት የመንግስት ተጠሪና የፖለቲካና ሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጉራሾ ለሚታ የሰነዱ ዋና ዓላማ ያለውን አጠቃላይ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ለመረዳት፣ ለመንቃት፣ ለመዘጋጀትና ፈተናን ወደ ዕድል ለመቀየር የሚያስችል አቅምን ማስታጠቅ ነው ሲሉ ገልጸው፤ እንደ ዓለም፣ እንደ ሃገር እና እንደ አካባቢ ለገጠሙን ችግሮች ምላሽ ለመስጠትና መፍትሔ ለማበጀት እንደ ስንቅ ይጠቅመናል ብለዋል።
በመጨረሻም የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ የተከበሩ አቶ ገለቦ ጎልቶሞ ፓርቲያችን ካስቀመጠው የመደመር እሳቤ አኳያ ዕይታችንን በማስፋት ለተፈጠሩ ችግሮች የመፍትሔ አካል መሆን ይገባል ያሉ ሲሆን፤ በሃሳብና በተግባር አንድ በመሆን በአካባቢ የገጽታ ግንባታ ላይ መስራት፤ ለዚህም አቅማችንን ማጎልበትና ከችግር በላይ ሆኖ በመሆን በማህበረሰቡ ውስጥ ያሉ ችግሮችን መቅረፍ ይጠበቅብናል በማለት አብራርተዋል።
በማጠቃለያውም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሺነር አቶ ሐልገዮ ጂሎ
አመራር ችግሮችን ወይም ፈተናዎችን ወደ ምቹ አጋጣሚ በመቀየሮ ለለውጥ የሚሰለፍ መሆን አለበት ሲሉ ገልጸው፤ ለኢትዮጵያ ችግር ኢትዮጵያዊ መፍትሔ እንደሚያስፈልግ ሁሉ ለአካባቢያችን ችግር አካባቢያዊ መፍትሔዎችን ለማበጀት አመራሩ በቁርጠኝነት ሊነሳ ይገባል ሲሉ ቀጣይ የስራ መመሪያ ሰጥተዋል።











