ትምህርት ለየትኛውም ችግር መፍትሄ በመሆኑ ለትምህርት ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ የኮንሶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ፍሬዘር ኮርባይዶ አስገነዘቡ፣


የኮንሶ ልማት ማህበር ከዞኑ አስተዳደር ጽ/ቤት እና ከዞኑ ትምህርት መምሪያ ጋር በመተባበር በ2016 የትምህርት ዘመን በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የሽኝት መርሃግብር አካሂዷል።
በመርሃግብር የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የኮንሶ ልማት ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሽብሩ ስካ እንደተናገሩት የኮንሶ ልማት ማህበር በኮንሶ ህዝብ የተቋቋመና ለኮንሶ ህዝብ የተሻለ ህይወት የሚተጋ የልማት ማህበር መሆኑን አስገንዝበዋል።

ልማት ማህበሩ ከመንግስት ጎን በመሆን በዞኑ በተለያዩ አካባቢዎች ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የገለፁት አቶ ሽብሩ፤ትምህርት ለአንድ ማህበረሰብ ሁለንተናዊ ለውጥ ያለው ፋይዳ በየትኛውም በዋጋ የሚተመን አይደለም ብለው ልማት ማህበሩ በሰፊው በትምህርት ዘርፍ እየሠራ የሚገኝ መሆኑን አስረድተዋል።
ዋና ስራ አስኪያጁ አቶ ሽብሩ አክለውም ተማሪዎቹ ባስመዘገቡት ከፍተኛ ውጤት በሚገቡበት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጠንክረው በመስራት በአካባቢያችን ለሚስተዋሉ ችግሮች ባለመፍትሄ መሆን እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
የኮንሶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ፍሬዘር ኮርባይዶ በበኩላቸው ትምህርት ለየትኛውም ችግር በራሱ መፍትሄ በመሆኑ ሁሉም ለትምህርት ከወትሮው የተለየ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስተዋለ ያለው የተማሪዎች ውጤት ማሽቆልቆል ለትምህርት ዘርፍ ትኩረት ያለመሰጠቱ ያመለከተ ነው ያሉት ኢንጂነር ፍሬዘር፤የማህበረሰብን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ትኩረት በመስጠት የትምህርት ዘርፉን ወደ ቀድሞ ዝና ለመመለስ መረባረብ ይጠበቅብናል ብለዋል።

የኮንሶ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የዞኑ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ መሣይ አሰፋ እንደተናገሩት ትምህርት ለኮንሶ ህዝብ ብቸኛ አመራጭ በመሆኑ በገቡበት ዩኒቨርሲቲ በቁጭት ሠርተው አመርቂ ውጤት በማስመዝገብ የአካባቢያቸውን ስም እንዲያስጠሩ አጽንኦት ሰጥተው መክረዋል።
የኮንሶ ዞን ረዳት የመንግስት ተጠሪና የዞኑ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ በርሻ ኦላታ እንደተናገሩት ሀገር በቀል የኮንሶ ልማት ማህበር ሰው ተኮር የሚለውን የብልጽግና መንግስት መሪህ በትምህርቱ ዘርፍ እያደረገ ባለው ርብርብ በተግባር እያረጋገጠ የሚገኝ ተቋም በመሆኑ ምስጋና ይገባዋል ሲሉ ተናግረዋል።
ሌሎች ሀሳብና አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው ተማሪዎች ከዚህ ቀደም ከሚሠሩት በይበልጥ ጠንክረው አቋም በመያዝ ውጤታማ መሆን እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
መማር ሙሉ ሰውን ያደርጋል ያሉት አስተያየት ሰጪ የመድረኩ ተሳታፊዎች፤ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎች በወጣትነት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ጊዜያቸውን ለሄዱበት ዓላማ ብቻ በመጠቀም ከአልባሌ ባህሪያት ራሳቸውን እንዲጠበቁ በአጽንኦት በሰፊው መክረዋል።

ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች በሰጡት አስተያየት የዞኑ መንግስትና የኮንሶ ልማት ማህበር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስተዋለ የተማሪ ውጤት ማሽቆልቆል ችግርን ለመቅረፍ እያደረጉ ያሉ ርብርብን አድንቀዋል።
ራሳችንን ከተማመን የማይቻል ነገር የለም ያሉት ተማሪዎቹ፤በቀጣይ ብሔራዊ ፈተና የሚፈተኑ ተማሪዎቻችን አሉታዊ አስተሳሰቦችን ከራሳቸው በማስወገድና በብሔራዊ ፈተና ዙሪያ የሚስተዋሉ ከተሳሳቱ አመለካከቶች ራሳቸውን በማራቅ እንዲሁም ሁለንተናዊ ትኩረታቸውን በትምህርት ላይ አድርገው የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የኮንሶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ፍሬዘር ኮርባይዶ በማጠቃለያቸው ዛሬ አመርቂ ውጤት ያስመዘገባችሁ የወደፊት የዞናችን ሀብት መሆናችሁን ተገንዝባችሁ ማህበረሰባዊ ዕውቀትና ባህልን በመላበስ ሙሉ ሰው ሆናችሁ የማህበረሰባችንና የአካባቢያችንን ችግር ፈቺ ከመሆናችሁም በተጨማሪ አካባቢያችንን በመልካም ስም የሚታስጠሩም ጭምር ልትሆኑ ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል።
በመጨረሻም በአጠቃላይ በኮንሶ ዞን በ2016 የትምህርት ዘመን በማህበራዊና በተፈጥሮ ሳይንስ 50 በመቶ እና ከዚያ በላይ ያስመዘገቡ ተማሪዎች 109 መሆናቸው የተገለፀ ሲሆን ከ350 በላይ ውጤት ላስመዘገቡ 45 ተማሪዎች የማበረታቻ የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
የኮንሶ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉ/መምሪያ
ጥቅምት 19/2017 ዓ/ም







