ቤተሰቦቹን በአሰቃቂ ሁኔታ በጥይት ደብድቦ የገደለ ወንጀለኛ በሞት ፍርድ እንዲቀጣ የኮንሶ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ ወንጀል ችሎት አስታወቀ።
የወንጀል ድርጊት የፈፀመው አቶ ከፍታ ካፋላ ወዳጆ በጋርዱላ ዞን የሃይበና ቀበሌ ነዋሪ ሲሆን የግድያ ወንጀሉን የፈፀመው በኮንሶ ዞን ሠገን ዙሪያ ወረዳ ሠገን ገነት ቀበሌ ሣጋንቶቴ ንዑስ መንደር መሆኑን ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ በቀረቡት የክስ ማስረጃዎች አረጋግጧል።
ተከሰሽ አቶ ከፍታ ካፋላ 3 ቤተሰቦቹን በመግደልና አንዱን በማቁሰል ወንጀል የተከሰሰ ሲሆን በአራቱም ወንጀሎች ጥፋተኛ መሆኑንም አምኖ ድርጊቱን የፈጸመው ከወላጅ አባቱ ጋር በጥቅም አለመግባባት መነሻ መሆኑን ጠቅሷል።
አቶ ከፍታ ካፋላ የገዛ አባቱ አቶ ካፋላ ወዳጆ፣ እናቱን ወ/ሮ ካሰች ሉታይቶ እና የአባቱ ወንድም አቶ አለሙ ወዳጆ የተባሉትን ግለሰቦች በአሰቃቂ ሁኔታ በጥይት ደብድቦ በመግደል ውሳኔ ተላልፎበታል።
በተጨማሪም የ9 ዓመት ዕድሜ ያለው ወንድሙን ታዳጊ ለውጠኝ ካፋላን በጥይት ማቁሰሉን ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ በክስ ማስረጃዎች አረጋግጦበታል።
ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ በህጉ መሠረት የቅጣት ማክበጃ ወንጀሎችን በመመርመር ግለሰቡ አምስት የቅጣት ማክበጃ ነጥቦች መፈፀሙንም ከፍተኛ ፍ/ቤቱ አረጋግጧል።
ወንጀለኛ አቶ ከፍታ ካፋላ ወዳጆ በፈፀመው ጭካኔ የተሞላበት ጊዲያ ወንጀል ድርጊት በመሆኑ በሞት ፍርድ እንዲቀጣ የኮንሶ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት ወስኗል።
እንደዚህ አይነት የወንጀል ድርጊቶች በኮንሶ ማህበረሰብ ያልተለመዱና ፀያፊ በመሆናቸው ህብረተሰቡ ሰላም የመገንባት ዕሴት ላይ በትኩረት እንዲሰራና ወንጀል ድርጊቱን እንዲያወግዝ ፍርድ ቤቱ ያሳስባል።
መረጃው
የኮንሶ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉ/መምሪያ
ግንቦት 28/2016 ዓ.ም







