የፀጥታ ስጋቶችን ለመቅረፍና ዘላቂ ሠላምን ለመገንባት ሁሉም ልተባበር እንደሚገባ ተጠየቀ።


ሠላምን የሚያደፈርሱ ፀረ ሠላም ኃይሎችን ለማጋለጥ ህብረተሰቡ ሊረባረብ እንደሚገባም ተጠቁሟል።
በኮንሶ ዞን ኮልሜ ወረዳ እና በኧሌ ዞን ኮላንጎ ዙሪያ ወረዳ መካከል ያለው የፀጥታ ስጋትን በዘላቂነት ለመቅረፍ የሁለትዮሽ ምክክር መድረክ በኮንሶ ዞን ካራት ከተማ አካሂደዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ረዳት የመንግስት ተጠሪ አቶ ዳዊት ገበዬሁ እንደገለፁት ለአከባቢና ለህዝብ ሠላም የሁለቱም መዋቅር ዋና አስተዳዳሪዎችና የፀጥታ መዋቅሮች በመተባበር የታየውን ሰላም በዘላቂነት ማስቀጠል ያስፈልጋል ብለዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ወገኔ ብዙነህ በበኩላቸው በአካባቢው ያለው የፀጥታ ስጋት ለበርካታ ዓመታት የቆየ ቢሆንም በአብሮነት የተገነባ ሠላምን ለማጠናከር የሁለቱ መዋቅር አስተዳዳሪዎች በኃላፊነት ሊመሩ ይገባል ብለዋል።
በአካባቢው የሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮች ከመዋቅሮቹ አመራሮች አቅም በላይ ሊሆኑ አይገባም ያሉት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል መከላከል ምክትል ኮሚሽነር ደግፌ ደበላ፤ ችግሮችን ለመፍታትና የህዝቡን ሠላም ለማስጠበቅ የፀጥታ ኃይል፣ የዞኖችና የወረዳዎች አመራሮች ከህዝቡ ጋር በቅንጅት ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አርሻሎ አርካሌ በበኩላቸው የመንገድ ላይ ዘረፋዎችን በመለየት ወንጀለኞችን በህግ ቁጥጥር ስር በማዋል የታየውን ዘላቂ ሰላም ማስቀጠል ያስፈልጋል ብለዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ረዳት የመንግስት ተጠሪ አቶ ዳዊት ገበዬሁ ወንጀለኞችን ማጋለጥና በህግ ማስጠየቅ፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችን ማጠናከርና ለሠላም ኮሚቴዎች ምቹ ሁኔታን መፍጠር፣ ህዝቡ ፊቱን ወደ ልማት እንዲያዞር ለማድረግ በሁሉም ዘንድ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል።
መረጃው
የኮንሶ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉ/መምሪያ
ግንቦት 11/2016 ዓ/ም







