7ኛው ሀገራዊ ጠቅላላ ምርጫ በድል መጠናቀቁን ተከትሎ “ልማትን በማስቀጠል ብልጽግናን እናረጋግጥ!” በሚል መሪ ቃል የምስጋና መርሃግብር በቱራይቴ–ፓታንካልቶ ሰፈር ተካሄደ፣

ካራት፣ ሐምሌ 12/2018 ዓ.ም. (ኮንሶ ዞን ኮሙኒኬሽን)
“ልማትን በማስቀጠል ብልጽግናን እናረጋግጥ!” በሚል መሪ ቃል በኮንሶ ዞን ካራት ከተማ አስተዳደር ቀበሌ 02፣ ቀጠና 05፣ ሰፈር 02 የቱራይቴ–ፓታንካልቶ ብልጽግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ህዝቡ ላሳየው ድጋፍና ተሳትፎ የምስጋና መርሃ ግብር አካሂዷል።
መርሃ ግብሩ በአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች ምርቃትና ቡራኬ የተጀመረ ሲሆን፣ የክልል፣ የዞን፣ የከተማና የሰፈር አመራሮች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ ሽማግሌዎችና የህብረተሰቡ አባላት በሰፊው ተሳትፈዋል።
የሰፈሩ ዋና አስተዳዳሪ አቶ እርዳቶ ሶካ በንግግራቸው፣ ቱራይቴ–ፓታንካልቶ ሰፈር በካራት ከተማ ከሚገኙ ሰፈራት ውስጥ አንዱ ሲሆን ህዝቡ ሰላም ወዳድ፣ ልማትን አስቀዳሚ እና ሰውን አክባሪ ህብረተሰብ የሚኖርበት አንዱ ሰፈር መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም የነበሩ አለመግባባቶችን በመተው በአንድነት በመቆም በልማት ስራዎች አርአያነቱን ያረጋገጠ ሰፈር መሆኑንም አመላክተዋል።
በሰፈሩ ህዝብ፣በመንግስትና በአጋር ድርጅቶች የተገነቡ የእድር ጽሕፈት ቤቶች፣ የጣሪያ ላይ የውሃ ማጠራቀሚያዎች፣ ሻዎር መታጠቢያዎች፣ ለአቅመ ደካሞችና ለወላጅ አጥ ህፃናት የሚያገለግሉ ማዕከላት ግንባታ ስራዎች ለሌሎች ሰፈራት ልምድ የምቀመርበት አኩሪ ተግባራት መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ህዝቡ ያሳየው አንድነትና የሰላም ተምሳሌት ተሳትፎ ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ ድል እንዲያስመዘግብ ያደረገ መሆኑን በማውሳት፣ ለሀገር ሽማግሌዎች፣ ለሀይማኖት አባቶች፣ ለወጣቶች፣ ለሴቶችና ለመላው ህብረተሰብ ምስጋና አቅርበዋል።
የቱራይቴ-ፓትንካልቱ ሰፈር ብልጽግና ፓርቲ ኃላፊ አቶ ደስታ ተስፋዬ በበኩላቸው፣ የዘንድሮው 7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ከቀደሙት ምርጫዎች በተለየ ሁኔታ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ተዓማኒ ሆኖ መጠናቀቁ የህዝቡ አንድነትና የፖለቲካ ብስለት ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
በቱራይቴ–ፓታንካልቶ ሰፈር የተመዘገበው የህዝብ ተሳትፎና ለብልጽግና ፓርቲ የተሰጠው ድጋፍ የአካባቢውን አንድነትና የልማት ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።
ከምርጫው በኋላም ትኩረት ለልማት፣ ለሰላም እና ለመልካም አስተዳደርን በማጠናከር ላይ ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበው፣ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን በህዝብ ተሳትፎ በማጠናከር የብልጽግና ጉዞን እውን ማድረግ ከሁሉም እንደሚጠበቅ አሳስበዋል።
የካራት ከተማ ከንቲባ አቶ ጋሻው ኩሲያ በበኩላቸው፣ በሰፈሩ የታየው አንድነትና የምርጫ ውጤት ለሌሎች አካባቢዎች ተሞክሮ የሚሆን መሆኑን ገልጸው፣ የልማት ስራዎችን በመቀጠል ህዝቡ ያለውን አንድነት እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።
የኮንሶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ክቡር አቶ ገለቦ ጎልቶሞ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር፣ 7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ተዓማኒ ሆኖ በመጠናቀቁ ኢትዮጵያ ታላቅ ድል ማስመዝገቧን ገልጸው፣ ይህ ድል የህዝብ አንድነትና የጋራ ጥረት ውጤት መሆኑን አስረድተዋል።
አቶ ገለቦ አክለውም፣ የምርጫው ድል መጨረሻ ሳይሆን የበለጠ ልማትና የመልካም አስተዳደር ጉዞ መነሻ መሆኑን ጠቅሰው፣ በወንድማማችነትና በእህትማማችነት መንፈስ እጅ ለእጅ በመያዝ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን በጋራ ማስቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል።
የሰፈሩ አመራሮች ያቀረቧቸው የመብራት፣ የውሃ፣ የመንደር አደረጃጀትና ሌሎች የልማት ጥያቄዎችም በትብብር እንደሚፈቱ ገልጸዋል።
በመርሃ ግብሩ የልማትና የህብረተሰብ አንድነት ስራዎች ላይ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦችና ተቋማት የእውቅና ሽልማት የተሰጠ ሲሆን፣ በመድረኩ የኮንሶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ክቡር አቶ ገለቦ ጎልቶሞ፣ የዞኑ የፊት አስተባባሪዎች፣የዞኑ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ ገልገሎ ኦቶማ፣ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ሙሃባ ቃውያን ጨምሮ የክልል፣ የዞን፣ የከተማ አስተዳደሩና የሰፈሩ አመራሮች ተገኝተዋል።










