በኮንሶ ዞን የካራት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ 5ኛ ዙር የሠልጣኞች ምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ የኮንሶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ክቡር አቶ ገለቦ ጎልቶሞ ያስተላለፉት መልዕክት

ካራት፣ ሐምሌ 16/2018 ዓ.ም. (ኮንሶ ዞን ኮሙኒኬሽን)
በካራት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ 5ኛ ዙር የሠልጣኞች ምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ የኮንሶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ክቡር አቶ ገለቦ ጎልቶሞ ያስተላለፉት መልዕክት ፣
ክቡር አቶ ገለቦ ጎልቶሞ በካራት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ 5ኛ ዙር የሠልጣኞች ምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ለተመራቂዎች፣ ለወላጆች፣ ለመምህራን፣ ለክብር እንግዶችና ለኮሌጁ ደጋፊ ባለድርሻ አካላት ያስተላለፉትን መልዕክት በማስጀመር፣ በዚህ የደስታ ቀን በመገኘታቸው ታላቅ ኩራትና ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸው ለሁሉም ተመራቂዎች “እንኳን ደስ አላችሁ” ብለዋል።
በመልዕክታቸውም እንደገለጹት፣ ኮንሶ በትጋትና በሥራ ወዳድነት የሚታወቅ ቢሆንም ለረጅም ጊዜ የከፍተኛ የሙያ ትምህርት ተቋም ባለመኖሩ ተማሪዎች ለከፍተኛ ወጪና ችግር ይጋለጡ ነበር።
ይህን ለመቅረፍ በ2007 ዓ.ም. የተቋቋመው ኮሌጅ በአሁኑ ጊዜ ወደ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በማደግ ወጣቶችን በቅርበት የሙያ ክህሎት እንዲያገኙ እያስቻለ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የዘንድሮው 5ኛ ዙር ምረቃ ኮሌጁ በፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅነት ከተደራጀ በኋላ የተካሄደ የመጀመሪያ ምረቃ መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው ገልጸው፣ ኮሌጁ የደረሰበት ደረጃ የባለድርሻ አካላት ትብብርና የአመራሩ ጥረት ውጤት መሆኑን አስታውሰዋል።
በቀጣይም ኮሌጁን ወደ ሳታላይት ኢንስቲትዩት ደረጃ ለማሳደግ አዳዲስ የሙያ ዘርፎችን በመጨመርና የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ድጋፍ በማጠናከር እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልዕክት፣ ምረቃቸው የትምህርት ጉዟቸው መጨረሻ ሳይሆን የአዲስ የሥራ ምዕራፍ መጀመሪያ መሆኑን ጠቅሰው፣ የሥራ ፈላጊ ሳይሆኑ የሥራ ፈጣሪ፣ ፈጠራ አበልፃጊና ችግር ፈቺ እንዲሆኑ አሳስበዋል።
ታማኝነት፣ ትጋትና ሀገር ወዳድነትን በመርህ በመያዝ ለኮንሶ፣ ለክልሉና ለኢትዮጵያ እድገት የሚጠቅሙ ዜጎች እንዲሆኑም ጥሪ አቅርበዋል።
በመጨረሻም ለኮሌጁ እድገት አስተዋጽኦ ላበረከቱ የፌዴራል፣ የክልልና የዞን መንግሥት ተቋማት፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ በተለይም ለኮሌጁ የውሃ ችግር መፍትሔ ድጋፍ ላደረገው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምስጋና አቅርበው፣ ትብብሩ በቀጣይም እንዲጠናከር ጠይቀዋል።
“በድጋሚ እንኳን ደስ አላችሁ! መልካም የሥራና የስኬት ጊዜ ይሁንላችሁ። አመሰግናለሁ!” በማለት መልዕክታቸውን አጠናቀዋል።
በጊያ ግና







