“ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቶች ለጠንካራ ዲሞክራሲያዊ ባህል ግንባታ” በሚል መሪ ቃል ለፖለቲካ ፓርቲዎች የእውቅናና የምስጋና መርሃ ግብር ተካሂዷል።

ካራት፣ ሐምሌ 3/2018 ዓ/ም (ኮንሶ ዞን መ/ኮ/አገልግሎት)
በመድረኩ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የኮንሶ ዞን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጸሐፊና የኢዜማ ፓርቲ ተወካይ አቶ ከበደ ሃብት፣ 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ በሰላምና በስኬት በመጠናቀቁ መላውን የኮንሶ ህዝብ እንኳን ደስ አላችሁ በማለት የመርሃ ግብሩን ታዳሚዎች በደህና መጡ ብለዋል።
አክለውም አቶ ከበደ ፣ የጋራ ምክር ቤቱ በራዕው መሠረት በሀገራዊ እና አከባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የውይይት መድረኮችን በማመቻቸት፣ የህግ በላይነትን በማስፈን ሰላም እና መረጋጋት እንዲፈጠር በማስቻል፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሃላፊነት እንዲንቀሳቀሱ ለማድረግ የሚያስችል የጋራ መድረክ ስልት በመፍጠርና በመንደፍ ቀሪው ተግባሮች እንደሆኑ የሚመለከተው አካል ሁሉ እንዳውቀው አሳስበዋል ::
የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኮንሶ ዞን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢና የኢዲሕ ፓርቲ ተወካይ አቶ ታጋይ አድሱ በበኩላቸው፣ 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ በኮንሶ ዞን በሰላም፣ በዴሞክራሲያዊ መንገድና በመቻቻል መካሄዱ የሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የመንግሥት አካላት፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የህብረተሰቡ የጋራ ጥረት ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።
በቀደሙት ምርጫዎች የታዩ ክፍፍሎችና ግጭቶች እንዳይደገሙ የተቋቋመው የጋራ ምክር ቤት በዞን፣ በወረዳና በቀበሌ ደረጃ በቅንጅት በመስራት ግጭቶች በውይይት እንዲፈቱና የህዝቡ ሰላምና አንድነት እንዲጠበቅ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ጠቅሰዋል።
የምርጫው ውጤት በህዝብ ውሳኔ መወሰኑ ለጠንካራ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መሠረት መሆኑን በመግለጽ፣ ከምርጫ በኋላ ሁሉም ፓርቲዎች የፖለቲካ ልዩነታቸውን በሰላማዊ መንገድ በማስተናገድ ለሰላም፣ ለአንድነትና ለልማት በጋራ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በመጨረሻም የኮንሶ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጉራሾ ጎስኬ ባስተላለፉት መልዕክት፣ 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ በዞኑ በሰላምና በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትን ጨምሮ የሁሉም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረት ውጤት መሆኑን ገልጸው፣ የተጀመረው የመቻቻልና የውይይት ባህል በቀጣይም ተጠናክሮ በመቀጠል የዴሞክራሲ ሥርዓቱን ማጠናከርና ለህዝብ ጥቅም በጋራ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች፣ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ ስሆን ለፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የእውቅናና የምስጋና ምስክር ወረቀት ተሰጥቶ፣ መርሃ ግብሩም በጋራ ማዕድ በመጋራት ተጠናቋል።
በጊያ ግና








