#Ethio_Konso በኮንሶ ዞን ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ በ2016 የክረምት ወራት በወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ32 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ሀብት ማትረፍ መቻሉን አስታወቀ፣

በኮንሶ ዞን ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ የ2016 የክረምት ወራት ወጣቶች በጎ ፈቃድ የማጠቃለያ እንዲሁም የ2017 የበጋ ወራት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር አካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ የኮንሶ ዞን ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ምክትልና የወጣቶች ዘርፍ ኃላፊ ቀሲስ ከበደ ገለቱ እንኳን ደህና መጣችሁ ብለው በመልካም ስብእና የታጠሩ ወጣቶችን ለማፍራት በጎነትን ማስፋት ያስፈልጋል ብለዋል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በገንዘብ ብቻ የሚተመን ሳይሆን በስብእና ግንባታ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው እና ዘር ቀለም የማይገድበው በፈጣሪ ዘንድም ትልቅ ዋጋ የሚያሰጥ እንደሆነ ገልጸዋል።
የኮንሶ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የዞኑ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ መሳይ አሰፋ በበኩላቸው የበጎ ስራ ተግባራት ሊለመድ የሚገባ ተግባር ነው ብለዋል።
በዞኑ በተለያዩ መዋቅሮች የአቅመ ደካማ ቤቶችን በመገንባትና የተለያዩ የመንገድ ስራዎችን በመስራት በርካታ ሀብት ማትረፍ መቻሉን የገለጹት ምክትል አስተዳዳሪው አቶ መሳይ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደመንግስት በጎ ተግባራትን በሚያከናውኑ አካላት ጎን በመቆም አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግም ተናግረዋል።
የኮንሶ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት የፖለቲካ እና ርእዮተ አለም ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ የውብዳር ኦላታ ከተባበርን በርካታ ስራዎችን መስራት እንደምንችል ተናግረው፣ ለተግባሩ ትኩረት በመስጠት ወሰን ተሻጋሪ ተግባራት፣ በተለይ ከሴቶች እና ህጻናት ጋር የተያያዙ ስራዎች በትኩረት እንዲሰራባቸውም አስገንዝበዋል።
የክረምት ወራት ወጣቶች በጎ ፈቃድ የማጠቃለያ ሪፖርት እንዲሁም የ2017 ዓ.ም የበጋ ወራት የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት መነሻ እቅድ ያቀረቡት የኮንሶ ዞን ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ምክትል ኃላፊ ቀሲስ ከበደ ገለቱ 30,906 ሰዎችን በማሳተፍ ከ77ሺ በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን እና 44,044, 341 ብር ለማዳን ታቅዶ 32,486, 240 ብር የሚገመት ሀብት ማትረፍ መቻሉን በዝርዝር አብራርተዋል።
እንዲሁም ከ2017 ዓ.ም የበጋ በጎ ፈቃድ ስራዎች መነሻ እቅድንም በተመለከተ በ15 ዘርፎች በትምህርት፣ በአከባቢ ጥበቃ፣ በጤና፣ በመንገድና ትራንስፖርት በሰላም ግንባታ እና በሌሎችም ዘርፎች በርካታ ስራዎች ለመስራት መታቀዱን ገልጸው በዘንድሮው አመት ከ36 ሺ በላይ በጎ ፍቃደኞችን ለማሳተፍ መታቀዱን ቀሲስ ከበደ አብራርተዋል።
የተሰሩ ስራዎች አስደሳች ናቸው በይበልጥ ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ያሉት ተሳታፊዎች በአስተያየታቸው የወጣቶች ማእከላትን ማጠናከር እንደሚገባ፣ ከሰላም እሴት ግንባታ ጋር ተያይዞ መንግስት ሰፊ ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ እና ከትውልድ የስብእና ግንባታ አንጻር በርካታ ስራዎችን ለመስራት መነሳት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
በመርሀ ግብሩ የሃይማኖት አባቶች፣ የዞኑ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የመምሪያ እና የጽህፈት ቤት ኃላፊዎችና የበጎ አድራጎት ማህበራት የተሳተፉ ሲሆን በመድረኩ የኪነት ቡድን ጭፈራ እና የተለያዩ ትርኢቶች እንዲሁም ግጥሞች ቀርበው፣ ለሲቪክ ማህበራት፣ ለበጎ አድራጎት ማህበራት፣ ለግል ተቋማት፣ ለመንግስት ተቋማት፣ እንዲሁም የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ግለሰቦች እና ለአመቱ በጎ ሰው የእውቅና ምስክር ወረቀት፣የዋንጫ እና የሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
መረጃው
የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉ/መምሪያ
ጥቅምት 26/2017











