________
ዘርፈ ብዙ የክትባት አቀራረብ በአንድ ጊዜ የሚከናወን ተግባር አይደለም ያሉት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ የክትባት አስተባባሪ አቶ ተካልኝ ሳህሌ የዜሮ ዶዝ ክትባት፣ የቫይታሚን፣ የምግብ እጥረት ልየታ ስራዎች በቤት ለቤት አሰሳ እንደሚካሄድ አስታወቁ።
የክትባት ተግባራቱ በቅንጅት የሚያከናውኑት ይሆናል ያሉት በUNICEF ኢትዮጵያ የክትባት ስፔሻሊስት ሲስቴር አልማዝ መርዶክዮስ፤ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ቡድን፣ የጤና ባለሙያዎች፣ የሴቶች ልማት አደረጃጀቶች፣ የወረዳው ወይም የቀበሌ አስተባባሪዎች ትኩረት ሰጥተው ጥራት ላሌው ክትባት ተደራሽነትን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል ብለዋል።
በUNICEF ሀዋሳ ቢሮ የማህበራዊ ባህሪይ ለውጥ ባለሙያ አቶ ልዑል ስራጅ በበኩላቸው የጤና ባለሙያዎች ስለ ዜሮ ዶዝና በማህበረሰቡ ባህሪይ ለውጥ ዙሪያ ጠንካራ የኮሚኒኬሽን ስርዓት መፍጠር እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል።
በጤናና በወሳኝ ኩነት መካከል የመረጃ መጣረስ ሊኖር አይገባም ያሉት በUNICEF ሀዋሳ ቢሮ የጤና ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ሰለሞን ገላው በበኩላቸው የተገመገመ የመረጃ ፎርማትን በመጠቀም አስፈላጊውን መረጃ ለሚመለከተው አካል በማድረስ ማህበረሰቡን ሊለውጥ የሚገባ ስራን መስራት ይኖርብናል ብለዋል።
ለልየታ የሚያገለግሉ የወሳኝ ኩነት መረጃዎችን ለማግኘት የሚገጥሙ ችግሮችን መቅረፍ ያስፈልጋል ያሉት አስተያየት ሰጪ ተሳታፊዎች፤ በጤና ተቋማትና በወሳኝ ኩነት ሴክተር ያሉ የዘርፉ ባለሙያዎች በትኩረት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
በምክክር መድረኩ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሚከናወኑ ዘርፈ ብዙ የክትባት አቀራረብ የዜሮ ዶዝ ክትባት፣ የቫይታሚን፣ የምግብ እጥረት ልየታ ሰነዶች ዙሪያ መግባባትን በመፍጠር ውይይቱን አጠናቀዋል።
መረጃው
የኮንሶ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉ/መምሪያ
መጋቢት 27/2016 ዓ/ም







