የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ለከተማችን ውበት ከመስጠት ባሻገር ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ውስጥ የሚኖረው ፋይዳ የጎላ በመሆኑ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያበረክት እንደሚገባ ተገለፀ፣










የካራት ከተማ ነዋሪዎች የኮሪደር ልማት ኢንሼቲቭ በጠቅላይ ሚኒስቴራችን በአዲስ አበባ ተጀምሮ ውጤታማ በመሆኑ ወደ ሁሉም አካባቢዎች እንዲስፋፋ መደረጉ የከተሞች ውበት እንዲጨምር ማስቻሉን ገልጸዋል።
ነዋሪዎቹ አክለውም ልማቱ ከተማችንን ከሌሎች ከተሞች የተሻለችና ተወዳዳሪ ከማድረግ በተጨማሪ ለኢንቨስትመንት ምቹ ያደርጋል ያሉ ሲሆን፣ በከተማችን የኮሪደር ልማት መጀመሩ እጅግ በጣም አስደስቶናል ሲሉ ገልጸዋል።
በከተማችን እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ከተጠናቀቀ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን እናገኛለን ያሉት አስተያየት ሰጪ የከተማይቱ ነዋሪዎች አሁን ባለው ደረጃ ለወጣቶች የስራ ዕድልን ከመፍጠሩ በተጨማሪ የህብረተሰባችንን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማረጋገጥ የሚኖረው ፋይዳ የጎላ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ባለን አቅም የመደገፍ ተግባርን እንቀጥላለን ሲሉ ተናግረዋል።
የከተማችን ውበት የህዝባችን ውበት ነው ያሉት ነዋሪዎቹ፣ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ስራ ሳይስተጓጎል ቀጣይነት ባለው መልኩ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ የኮንሶ ማህበረሰብ የሆንን ሁላችንም በዕውቀት፣ በገንዘብ እና በጉልበት በመሳተፍ ታታሪነታችንን በተግባር ማሳየት ይጠበቅብናል ሲሉ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።
የካራት ከተማ ከንቲባ ኢንጂነር ያቤሎ ኩሴ በበኩላቸው ካራት ከተማ የዞኑ መዲና ከመሆኗ በተጨማሪ የክልል መቀመጫ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ ጠቅላይ ሚኒስትራችን በሀገር ደረጃ ባስጀመሩት የኮሪደር ልማት ኢንሼቲቭ ከተማውን ማልማት ይጠበቅብናል ብለዋል።
በካራት ከተማ እየተሠራ ያለው የኮሪደር ልማት አሁን ያለበት ደረጃ ሊደርስ የቻለው በከፍተኛ የህብረተሰብ ተሳትፎ መሆኑን የገለፁት ከንቲባው ህብረተሰቡ ለስራው የሚፈለጉ ይዞታዎችን ከመልቀቅና ንብረቶችን በራስ ተነሳሽነት ከማንሳት በተጨማሪ ልማቱን ማፋጠን ይቻል ዘንድ በገንዘብና በቁሳቁስ እየደገፈ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
ልማቱን ከመነሻው ጀምሮ አመራሩ፣ የመንግስት ሠራተኛው እንዲሁም በክልሉ የኮንሶ ማዕከልን ጨምሮ እንደ ቢሮ በየደረጃጀቱ የራሳቸውን አሻራ እያኖሩ ያሉበት ሁኔታ መኖሩን የጠቆሙት ኢንጂነር ያበሎ፣ የተጀመረው ልማት ከግብ እንዲደርስ አጠቃላይ ማህበረሰቡን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በገንዘብ፣ በጉልበት እና በእውቀት እያደረጉ ያሉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
የኮንሶ ዞን መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉ/መምሪያ ጥር 22/2017 ዓ.ም






