በኮንሶ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ “በጎነትና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ-3” በሚል መሪህ ቃል የ2016 የክረምት ወራት የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መድረክ ተካሂዷል።
______________
የኮንሶ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ምክትልና የወጣቶች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ቃይራኔ ቃንጫሮ በእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸው እንደገለፁት ወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዓላማና ጥቅምን ተገንዝበው ያለ ምንም ክፍያ በዕውቀትና በጉልበታቸው አቅመ ደካሞችን በመርዳት መልካም ዕሴት መገንባት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
መድረኩን በንግግር ያበሰሩት የኮንሶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ፍሬዘር ኮርባይዶ በበኩላቸው በጎነት መንፈሳዊ ጥበብ እንደሆነና እየተሸረሸረ የመጣውን የመረዳዳት ዕሴትን መልሶ ለማጠናከር የጎላ ሚና እንዳለው አስረድተዋል።

ወጣቶች ባላቸው ዕውቀትና ጉልበት ያለ ማንም ግፊት በራሳቸው ስሜትና ፍላጎት ሁለንተናዊ በጎነትን በሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች ራሳቸውን መስጠት ይጠበቅባቸዋል ያሉት ኢንጂነር ፍሬዘር፤ በአካባቢያችን በሚደረጉ የልማት ስራዎች ላይ ከመሳተፍ በተጨማሪ ድጋፍ ለሚሹ አካላት በበጎነት መሳተፍ ይኖርባቸዋል ብለዋል።
የኮንሶ ዞን ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ ሐመር ሀንሻ እንደተናገሩት በጎነት ከብልፅግና ተግባር ተኮር ተግባራት መካከል አንዱ መሆኑን ያስረዱት ሲሆን ሁሉም መዋቅሮች በታቀደው ዕቅድ መሠረት ወደ ተግባር በመግባት ይገባል ብለዋል።

በበጎነትና በአብሮነት ሀገርን መለወጥ እንችላለን ያሉት የኮንሶ ዞን ምክር ቤት ዋና አፌ ጉባኤ የተከበሩ አቶ ገልገሎ ኦቶማ፤ ለሠላም ዕሴት ግንባታ፣ ለትምህርት፣ በጤና፣ በግብርናና ገቢ አሰባሰብ ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥተን በንቅናቄ መረባረብ ይጠበቅብናል ብለዋል።
የኮንሶ ዞን ረዳት የመንግስት ተጠሪና የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ወንዱ ቦጋሌ ቦጋሌ በበኩላቸው ዛሬ ያስጀመርነው የክረምት ወራት ወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት በዞናችን የሚስተዋሉ ጉድለቶችን በመቅረፍ ሁሉም የበኩሉን አሻራ ሊያሳርፍ ይገባል ብለዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የቱሪዝም ዘርፍ ኃላፊ አቶ ገልገሎ ገልሾ እንደተናገሩት የክረምት ወራት በጎ ፈቃድ አገልግሎት “በጎነትና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ”! በሚል መሪህ ወደ ተግባር ከተገባ ጊዜ ጀምሮ በሀገር ደረጃ ከፍተኛ ለውጥ መምጣቱን ገልጸዋል።
የ2016 ዓ.ም የክረምት ወራት የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት መሪ ዕቅድ ሰነድ ያቀረቡት የኮንሶ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ምክትልና የወጣቶች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ቃይራኔ ቃንጫሮ በክረምቱ ወራት ወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት 79 ሺህ 868 ወጣቶችን በማሳተፍ 239 ሺህ 207 የህብረተሰብ ክፍልን ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን አስረድተዋል።
አረንጓዴ አሻራ ልማት፣ ድጋፍ የሚሹ አካላትን መደገፍ፣ ሠላምና ፀጥታ፣ ግብርና ልማት ስራ፣ ትምህርትና ስልጠና አገልግሎት፣ ጤና፣ መሠረተ ልማት ማጠናከርና ማልማት፣ መንገድ ደህንነትና የትራፊክ አገልግሎት የክረምት ተግባራት ዕቅዶች ናቸው።

አካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ፣ ጎጂ ልማዳዊና ፆታዊ ጥቃቶችን መከላከል፣ ስብዕና ግንባታ ስራ፣ ስፖርት መስክ፣ ክኔ ጥበብ ሙያ፣ ግብር አሰባሰብ ዙሪያ የንቅናቄ ትምህርት ተጨማሪ የክረምት ወራት ወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት የትኩረት መስኮች መሆናቸው አቶ ቃይራኔ በዕቅዱ ሰነድ አመላክተዋል።
ሀሳብና አስተያየት ሰጪ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በየመዋቅሮቻችን ያሉ የወጣቶችን እምቅ አቅምን በማስተባበርና በፍጥነት በዕቅዱ መሠረት ወደ ተግባር በመግባት ትኩረት ሰጥተን በመስራት ብዙ ሃብት ከማዳን በተጨማሪ ኮንሶን ብሎም ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ማማ ማሻገር እንችላለን ብለዋል።
የኮንሶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ፍሬዘር ኮርባይዶ በማጠቃለያ እንደገለፁት ለማህበረሰባችን የሚጠቅመው በጎነት ብቻ በመሆኑ ሁላችንም በበጎነት ተግባር ላይ የራሳችንን አሻራ በማሳረፍ ወደ ተግባር መግባት ይጠበቅብናል ሲሉ አሳስበዋል።
በካራት ከተማ አስተዳደር ኮሪያ ዶካቱ የአንድ አረጋዊ ቤት ግንባታ በመጀመር የ2016 የክረምት ወራት የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት በይፋ ተጀምሯል።
መረጃው
የኮንሶ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉ/መምሪያ
ሰኔ 25/2016







