ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ በኮንሶ ዞን ያሉ ታሪካዊ እና የቱሪዝም መዳረሻዎችን ጎበኙ፣

በጥንታዊ ታሪክና በድንቅ ሕይወት የተሞላ የደቡብ ኢትዮጵያ መሬት፣ በተለይ ደግሞ በኮንሶ ዞን የሚገኙ የተፈጥሮ እና በሰው እጅ የተዋቀሩ ድንቅ ቅርሶች ለዘመናት የማይረሱ ታሪኮችን በግልጽ ሁኔታ ይናገራሉ።
በዚህም መሠረት በካራት ከተማ አስተዳደር ጋሞሌ የሚገኙ አምባ መንደራት፣ ታሪካዊ የቱሪዝም መዳረሻዎችና ቅርሶች በደማቅ ሁኔታ ተጎብኝተዋል።
ጉብኝቱን ያካሄዱት የሰሜን ወሎና የደቡብ ወሎ ከሚሴ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ እና ሌሎች የሃይማኖት አባቶች ነበሩ።
ብፁዕነታቸው ከሌሎች የቤተ-ክርስቲያን አገልጋዮችና ከመንግሥት ኃላፊዎች ጋር በመሆን በአካባቢው ያሉ ታሪካዊ ቅርሶችን ተመልክተዋል።
በጉብኝቱ ወቅት ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ በኢትዮጵያ ያሉ ታሪካዊ ቅርሶች በሙሉ እንደሚያስደንቁ በመግለጽ፤ በኮንሶ ያዩት ልዩ የባህል እና የታሪክ ሀብት ግን በልዩ ሁኔታ እጅግ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።
እንዲሁም ቅርሶቹ ከሃይማኖት ጋር የማይጋጩ፣ ማህበረሰቡም ሰላማዊ፣ ፈጣሪን የሚፈራ እና ጥላቻን የማይወድ መሆኑን በተጨማሪነት የሚያመላክቱ ናቸውም ብለዋል።
ብፁዕነታቸው የኮንሶ ህዝብ የፈጠራና የህንፃ ጥበብ በአእምሮ፣ በአካል እና በጉልበት ተዋህዶ የተገነባ መሆኑን በመጠቆም፣ ይህ ባህላዊ ሀብት ለትውልድ መተላለፍ እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
በመጨረሻም “ቅርስ ተጠብቆ ሲኖር አገር ትጠበቃለች” በሚል መልእክታቸው ለኮንሶ ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያውያን ጥሪ በማቀረብ፣ በተለይ ወጣቶች በቅርስ ጥበቃ ላይ ከፍተኛ ሚና እንዲወጡ አሳስበዋል።
በጉብኝቱ ላይ የጋሞና አካባቢ ሕዝቦች፣ የጎፋና ባስኬቶ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ፣ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ ሊቀ ልቃውንት ዮሴፍ ደሳለኝ፣ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ እና ሌሎች የቤተ-ክርስቲያን አገልጋዮች፤ እንዲሁም የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች የተገኙ ስሆን፤ አባቶቹም በኮንሶ ያሉ ቅርሶችን በመመልከታቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።



ሚያዚያ 18/2018 ዓ.ም






