‹‹ቋንቋችን የማንነታችን መገለጫ ነው!›› –
ወ/ሮ የውብዳር ኦላታ – በኮንሶ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ረዳት የመንግስት ተጠሪ

ወ/ሮ የውብዳር ኦላታ – በኮንሶ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ረዳት የመንግስት ተጠሪ
‹‹ትውልዱ ቋንቋውን የመናገርና የማሳደግ አደራ አለበት!››
“ቋንቋችን ክብራችን፣ ለሁለንተናዊ ብልፅግናችን!” በሚል መሪ-ቃል የ“አፋ ኾንሶ” ቀን መከበር ጀመረ፣
የአንድ ማህበረሰብ ቋንቋ እንዲያድግና እንዲበለጽግ ትውልዱ ቋንቋውን በመናገርና በመፃፍ አደራውን ሊወጣ እንደሚገባ የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ፡፡
ቋንቋችን በመማር ማስተማሩ ሂደት ውስጥ ሊጠናከር ይገባል
ያሉት በመምሪያው የቋንቋና ስነ-ጥበብ ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገመቹ ገንፌ፣ ይህም ለህፃናትና ለታዳጊዎች መስጠት የተጀመረውን የቋንቋ ልማት ሥራ ያፋጥናል ሲሉ ተናግረዋል።
የመምሪያው ኃላፊ አቶ ሠራዊት ዲባባ በዞኑ ለ3ኛ ጊዜ የሚከበረው የ“አፋ ኾንሶ ቀን” ህፃናትና ታዳጊዎች አፋቸውን በቋንቋው እንዲፈቱ፣ እንደዚሁም ተተኪ ትውልድ የሆኑ ወጣቶች እና ተማሪዎች የቋንቋው ተናጋሪ እንዲሆኑ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡
ቋንቋውን የሚጽፍ፣ ሚናገርና የሚያሳድግ ትውልድ ለመፍጠር በየዓመቱ ቀኑን በማሰብ በልዩ ልዩ ኩነቶች በትኩረት ማክበር እንደሚገባም ኃላፊው አብራርተዋል፡፡
በመድረኩ የተገኙት ረዳት የመንግስት ተጠሪ እና የዕለቱ የክብር እንግዳ ወ/ሮ የውብዳር ኦላታ የ“አፋ ኾንሶ” ቀንን ስናከብር ለመርሃ-ግብር ፍጆታ ሳይሆን ለቋንቋ ልማት ዕድገት በመሆኑ ሁሉም ለዘርፉ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ብለዋል፡፡
ቋንቋችን የማንነታችን መገለጫ ነው ያሉት ወ/ሮ የውብዳር፤ ትውልዱ አባትና እናቱን ‹‹አፖ››፣ ‹‹አዬ››፣ ታላቁን ‹‹ታቴ››፣ አያቱን ‹‹ካካ›› እና ‹‹ኦኮዬ›› በማለት ከበሬታና ግብረ-ገባዊ ሥርዓቱን እንዲያጠናክር ተማሪዎችን መክረዋል፡፡
ትውልዱ ኮንስኛ ተናጋሪ በመሆን ቋንቋውን እንዲያሳድግና ባህሉን እንዲጠብቅ፣ በግብረ-ገብ ስርዓት የታነፀና ወላጆቹን የሚያከብር ትውልድና ዜጋ ለመቅረጽ የአከባቢን ባህልና ቋንቋ መጠበቅ ዋንኛ ተግባር እንደሆነም አስገንዝበዋል፡፡
በልዩ ልዩ ኩነቶች በመከበር የተጀመረው የ“አፋ ኾንሶ” ቀን በኮንሶ ከፍተኛ 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪዎች መካከል
በባህል፣ ታሪክና ቅርስ ዙሪያ በኮንሶኛ ቋንቋ የተዘጋጀ የጥያቄና መልስ ውድድር በማካሄድ ታስቦ ውሏል፡፡
በውድድሩ 32 ባህል አቀፍ ጥያቄዎች የተሰነዱ ሲሆን፤ አራት ሴት እና አራት ወንድ ተማሪዎች ተፎካክረው ከ1-3ኛ አብላጫ ውጤት ላስመዘገቡ የምስክር ወረቀትና በኮንስኛ የተዘጋጁ መጽሐፍት በሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
ከጥያቄ ዝግጅት ጀምሮ መድረኩ ሙሉ በሙሉ በኮንስኛ ቋንቋ ብቻ የተከናወነ ሲሆን፤ የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ፣ ተማሪዎች፣ መምህራን እና የባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሠራተኞች በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል፡፡
ማህበረሰቡ በሥራ ቦታና በመገበያያ ስፍራዎች ቋንቋውን በመናገር ለቋንቋው ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ መምሪያው ጠይቋል፡፡
በአባቶች ቡራኬ የተጀመረው የ‹‹አፋ ኾንሶ›› ቀን በኮንሶ ከፍተኛ 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ት/ቤት በድምቀት ተከብሮ ውሏል፡፡
መረጃው
የኮንሶ ዞን መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉ/መምሪያ
የካቲት 21/2017 ዓ.ም











