
ሰባተኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ በኮንሶ ዞን በሰላም መጠናቀቁን አስመልክቶ የኮንሶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ክቡር አቶ ገለቦ ጎልቶሞ የሰጡት መግለጫ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮንሶ ዞን የተካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ በሁሉም የምርጫ ክልሎችና ጣቢያዎች በሰላማዊ፣ በተረጋጋ፣ በፍትሃዊ እና ሥርዓት በተሞላ ሁኔታ ተጠናቋል።
ይህ ታላቅ ሀገራዊ ሂደት በስኬት እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላደረጉ የኮንሶ ዞን ሕዝብ ከልብ የመነጨ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።
በተለይም ከጠዋቱ 12:00 ሰዓት ጀምሮ በምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት የዴሞክራሲ መብታቸውን እና የዜግነት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ለተወጡ ሴቶች፣ ወንዶች፣ ወጣቶች፣ አረጋውያን፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ልጆቻቸውን ያቀፉ እናቶች፣ እርጉዝ እናቶች፣ የአካል ጉዳተኞች እንዲሁም መላው የኮንሶ ሕዝብ ልዩ ምስጋና ይገባዋል።
ምርጫው በሰላም እንዲካሄድ ለተጫወቱት ሚና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮንሶ ምርጫ ክልል ጽሕፈት ቤት፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች፣ የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴዎች፣ ታዛቢዎች እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ከፍተኛ ምስጋና ይገባቸዋል።
እንዲሁም የዞኑ የፀጥታ አካላት፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ፣ የኮንሶ ዞን ፖሊስ፣ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻዎች፣ የቀበሌ የሰላም አደረጃጀቶች እና ሌሎች የፀጥታ አካላት ሌት ተቀን በመሥራት ለምርጫው ሰላማዊ አካሄድ ያበረከቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው።
የፖለቲካ ፓርቲዎች እና እጩዎቻቸው የሕግ የበላይነትን በማክበር፣ የምርጫ ሥነ-ምግባርን በመከተል እና ችግሮች ሲፈጠሩ በውይይትና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያሳዩት ቁርጠኝነት ለምርጫው ስኬት ወሳኝ አስተዋፅኦ አበርክቷል።
በተጨማሪም የመንግሥት ተቋማት፣ የትምህርት ተቋማት፣ የመገናኛ ብዙኃን፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የሴቶችና የወጣቶች ማኅበራት፣ የሃይማኖት ተቋማት እና የማህበረሰብ መሪዎች ለሕዝብ ግንዛቤ በመፍጠርና ለሰላም በመስራት ያበረከቱት ሚና እጅግ የሚያስመሰግን ነው።
ይህ ስኬት የአንድ ተቋም ወይም የአንድ አካል ስኬት ሳይሆን፣ የኮንሶ ሕዝብ የጋራ ስኬት ነው ፣ የሰላም ባህላችንን፣ የመቻቻል እሴታችንን እና የጋራ ልማት ፍላጎታችንን በተግባር ያረጋገጥንበት ታሪካዊ አጋጣሚ ነው።
ከዚህ በኋላም የምርጫ ውጤት ምንም ይሁን ምን፣ የኮንሶ ሕዝብ የነበረውን የአንድነት፣ የመቻቻልና የሰላም መንፈስ በመጠበቅ ለዞናችን ልማትና እድገት በጋራ እንዲሰራ ጥሪዬን አቀርባለሁ።
ኮንሶ በምርጫው አሸናፊ ያደረገው ሰላምን፣ አንድነትን እና ዲሞክራሲያዊ ተሳትፎ ነው።
ክቡር አቶ ገለቦ ጎልቶሞ
የኮንሶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ






