
“ሰላም፣ ትብብርና የሕዝብ ንቁ ተሳትፎ የሰባተኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ስኬት መሠረቶች ናቸው” ሲሉ የኮንሶ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ
በኮንሶ ዞን የሰባተኛውን ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ በተመለከተ አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች፣ ምርጫው በፍጹም ሰላማዊ ሁኔታ መካሄዱ የሕዝቡ ንቁ ተሳትፎ፣ የፀጥታ አካላት ቁርጠኝነት፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች የተቀናጀ ሥራ እንዲሁም የማህበረሰቡ የትብብር መንፈስ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።
የካራት ከተማ ነዋሪ አቶ ሄኖክ በየነ በሰጡት አስተያየት፣ ምርጫው ዜጎች የፈለጉትን ፓርቲ በነፃነትና በፍትሃዊነት የሚመርጡበት ዴሞክራሲያዊ ሂደት መሆኑን ገልጸው፣ በአካባቢያቸው ምንም ዓይነት የጸጥታ ችግር አለመኖሩን እና ምርጫው ከቀደሙት ዙሮች የተሻለ ሰላማዊ ድባብ እንዳለው ገልጸዋል።
አቶ አብርሃም አበበ በበኩላቸው፣ ሕዝቡ በሚቀጥሉት ዓመታት ሀገሪቱን እንዲመራ የሚያምነውን ፓርቲ በነፃነት እየመረጠ መሆኑን ገልጸው፣ ይህም የዴሞክራሲ ግንባታን የሚያጠናክርና ለመልካም አስተዳደር መሠረት የሚጥል ሂደት መሆኑን ጠቁመዋል።
ወጣት ሶተ ገመዳ በበኩላቸው፣ በዚህ ዙር ምርጫ በወጣቶች መካከል የሚታየው የሥርዓት፣ የመተባበር እና የመታዘዝ መንፈስ እጅግ የሚያበረታታ መሆኑን ገልጸዋል። ከዚህ ቀደም ይታዩ የነበሩ አንዳንድ የሥርዓት ክፍተቶች በእጅጉ መቀነሳቸውን ጠቅሰው፣ ይህ ለወደፊቱ የተሻለ የምርጫ ባህል መሠረት እንደሚሆን አስረድተዋል።
የሚሊየም ሰፈር ነዋሪ ወ/ሮ ፋንቱ ኩሜዳ በሰጡት አስተያየት፣ የምርጫ ጣቢያዎች ለማህበረሰቡ ቀረብ ብለው በመዘጋጀታቸው ከዚህ ቀደም ይታዩ የነበሩ ረጃጅም ሰልፎችና መጨናነቆች በእጅጉ መቀነሳቸውን ገልጸው፣ መራጮች በቀላሉ ድምፃቸውን እየሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።
ሌሎች ነዋሪዎች፣ ሴቶች፣ አረጋውያን እና ወጣቶች በሰጡት አስተያየትም ሕዝቡ በሥርዓት ተሰልፎ ድምፁን እየሰጠ መሆኑን፣ የምርጫ ሂደቱም ያለምንም ስጋት እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።
በአጠቃላይ ነዋሪዎቹ እንደገለጹት፣ ሰባተኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ በኮንሶ ዞን በሰላም፣ በፍትሃዊነት፣ በሕዝብ ሰፊ ተሳትፎ እና በሁሉም አካላት ትብብር እየተካሄደ ሲሆን፣ ይህም የዲሞክራሲ ጉዞውን የሚያጠናክር አበረታች ምልክት መሆኑን አመልክተዋል።
መረጃው
የኮንሶ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
ግንቦት 24/2018 ዓ/ም






