
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የካራት ማዕከል ሠራተኞች እንዲሁም የዞኑ ባለድርሻ አካላት ጋር የኮንሶ ባህላዊ ቅርሶች መስክ ምልከታ አካሂደዋል።
ልዑካን ቡድኑ ምልከታውን ያካሄደው በከና ወረዳ እና ካራት ዙሪያ ወረዳ ነው።
የከና ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ካንታሌ ካፖሌ ልዑካን ቡድኑ በከና ወረዳ ኮንሶ ኒውዮርክ የተፈጥሮ ባህላዊ ቅርስን በሚጎብኙበት ወቅት እንኳን ደህና መጣችሁ ብለው ከና ወረዳ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ ቅርሶች መገኛ መሆኑን ገልጸዋል።
ባህላዊ ቅርሶች ለአንድ አካባቢ ያለው የኢኮኖሚ ጠቀሜታ የጎላ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ከማህበረሰቡ ጥበቃ በተጨማሪ የባህልና የቱሪዝም ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራበት ይገባልም ብለዋል።
የኮንሶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገልገሎ ገልሾ በበኩላቸው ኮንሶ ዞን የተለያዩ ጥንታዊ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ቅርሶች እንዲሁም የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች መገኛም ጭምር መሆኑን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ከሚሠራባቸው የትኩረት አቅጣጫዎች መካከል የቱሪዝም ዘርፍ አንዱ መሆኑን የተናገሩት አቶ ገልገሎ፤ የዞኑ መንግስት ቅርሶችን ለማልማት ዘርፈ ብዙ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ገልፀው የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።
ቅርሶችን ለማልማት የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ተቀርፀው ህዝቡን በኢኮኖሚው ዘርፍ ተጠቃሚ ሊያደርጉ ይገባል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው አቶ ገልገሎ፤ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የዘርፉ ባለሙያዎች ቅርሶቻችን በመጎብኘት ጥናትና ምርምር በማድረግ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ ያቀረቡት ሲሆን ቢሮው ቅርሶችን ለመጎብኘት ያደረገው ርብርብ ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የባህል ታሪክ ጥናትና ልማት ባለሙያ አቶ ሻካይቶ ሮባ እንደተናገሩት የኮንሶ ባህላዊ ቅርስ ከዓለም ቅርሶች መካከል አንዱ ነው ብለው የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በአቅራቢያው የሚገኘውን የቅርስ ጥበቃ ሁኔታን ለመገምገም ምልከታ ማካሄዱን አድንቀዋል።
የመስክ ምልከታ ዋና ዓላማ በቅርስ ጥበቃ ዙሪያ ያሉ ክፍተቶችን ለይቶ ማውጣትና አስፈላጊውን እርምጃ በመውሰድ የህዝቡን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን ማረጋገጥ ነው ሲሉ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ አቶ ሙሉነህ ተፈራ ተናግረዋል።
የቅርሱ ባለቤት እራሱ ማህበረሰቡ በመሆኑ ማህበረሰቡን በግንዛቤ በመገንባትና የቴክኒካል ድጋፎች እናደርጋለን ስሉ ተደምጠዋል።
ቅርስ ሳይኖር ስለ ቱሪስት ማሰብ አዳጋች ነው ያሉት አቶ ሙሉነህ፤ በአንዳንድ አካባቢ በቅረሶች ላይ ሰው ሠራሽ ጉዳቶች እየተስተዋሉ እንደሆኑና እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የስትራቴጂካዊ ዕቅድ አካል በማድረግ የኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንደሚሠሩም ገልጸዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትልና የባህል ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሚልኪያስ ካልሳ እንደገለጹት ካራት የክልሉ መቀመጫዎች መካከል አንዱ ከመሆኑም ባሻገር የዓለም ቅርስ መገኛ በመሆኑ አድንቀዋል።
የኮንሶ ህዝብ ሀገር በቀል ባህልና ዕውቀት ለዓለም ህዝብ ያስተማረ ህዝብ ነው ያሉት አቶ ሚልኪያስ፤ መቀመጫውን የቅርስ መገኛ ካራት ያደረገው ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በቅርሶች ጥበቃ የበኩሉን እየተወጣ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በመስክ ምልከታው የሚስተዋሉ ጉድለቶችን በመቅረፍና የታዩ ጠንካራ ጎኖችን ለማስቀጠል የታለመ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ልዑካን ቡድኑ በከና ወረዳ ኮንሶ ኒውዮርክ የተፈጥሮ ቅርስ፣ የካላ ጥብቅ ደን፣ በካራት ዙሪያ ወረዳ መጨሎ አምባ መንደርን ምልከታ አድርጓል።
በምልከታው የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከፍተኛ ኃላፊዎችና የቢሮው ማናጅመንት አባላትና ሠራተኞች፣ የኮንሶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገልገሎ ገልሾ፣ የዞኑ ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ ሻካይቶ ሳይሙሮን ጨምሮ ሌሎች የዞኑ ካቢኔ አባላት፣ የከናና የካራት ዙሪያ ወረዳ የፊት አስተባባሪዎች ተገኝተዋል።
መረጃው
የኮንሶ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉ/መምሪያ
መጋቢት 18/2016 ዓ/ም







