
ባለፉት አመታት ሀገራዊ ለውጡ የተደቀኑበትን ፈተናዎች ወደ ድል እየቀየረ በርካታ ስኬቶች አስመዝግቧል ሲሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ገልጸዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ የብልጽግና ፓርቲ 5ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፣ የለውጥ ጉዞው በኢትዮጵያ የነበረውን የፖለቲካ ስብራት በመጠገን ምህዳሩን በአዲስ ምዕራፍ የቀየረበት ነው ብለዋል።
በዚህ ሂደት ውስጥ ሀገራችን በርካታ ፈተናዎች ቢያጋጥማትም ፈተናዎችን ወደ ድል በመቀየር በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገብ መቻሉንም ገልጸዋል።
ገዢዉ ፓርቲ ላለፉት 5 የለውጥ ዓመታት በወሰዳቸው ዘርፈ-ብዙ እርምጃዎች የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋጥ ፅኑ መሰረት የሚሆኑ ድሎችን ማስመዝገቡንም ተናግረዋል።
ለውጡ ለክልሉ ህዝቦች የዘመናት ጥያቄዎች ሆነው የቆዩትን የአደረጃጀት፣ የልማት እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ምላሽ እየሰጠባቸው መሆኑንም ተናግረዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የለውጡ ትሩፋት ውጤት ነዉ ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉ ምስረታ ሂደት እውነተኛ የዴሞክራሲ ስርዓት አንዱ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በሀገራችን የፖለቲካ ታሪክ አጋር እና እህት የሚባል አግላይ የፖለቲካ አሰራርን በመሻር ሁሉም ባለቤት ሆኖ በጋራ የሚመራት ሀገር መፍጠር ተችሏል ብለዋል።
አዲስ የፖለቲካ ባህል ባስመዘገበ መልኩም ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጋራ ምክር ቤቶች ተቀራርቦ በመስራት ውጤት መምጣቱን ጠቁመዋል።
ርዕሰ-መስተዳድሩ ለመላው የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች መጪው ጊዜ የስኬት፣ የብልጽግናና የከፍታ እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል ሲል ከክልሉ መንግስት ኮሚኒኬሽን ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።







