በሩብ ዓመቱ ከ900 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ “በኮንትሮባንድና ህገ-ወጥ ንግድ መከላከል እና የኤክስፖርት ምርት ማነቆዎች” ዙሪያ የንቅናቄ መድረክ በኮንሶ ዞን ካራት ከተማ አካሂዷል።
በንቅናቄው መድረክ የኮንሶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ፍሬዘር ኮርባይዶ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፣ በዞኑ በባህልና ቱሪዝም፣ በንግድ፣ በግብርና እና በኢንቨስትመንት መስክ ያሉ እምቅ ፀጋዎችን ለተሳታፊዎች ገልጸዋል።
ኢንጂነር ፍሬዘር አክለውም ኮንትሮባንድና ህገ-ወጥ ንግድ ከሚያስከትለው የኢኮኖሚ ቀውስ ባሻገር ለቀጠናዊ ትስስር ስጋት የሆነና በሁለንተናዊ ዕድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ የሚገኝ ፀረ-ኢኮኖሚ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የ2017 በጀት የ1ኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት እና የኮንትሮባንድና ህገ- ወጥ ንግድ መከላከል ግብረ ሃይል አደረጃጀት እንዲሁም በኤክስፖርት ግብይትና አቅርቦት ላይ ያሉ ማነቆዎችን መፍታት የሚሉ ሰነዶች ከቀረቡ በኋላ በስፋት ውይይት ተደርጎባቸው ሀሳብና አስተያየቶች ተሰጥተውባቸዋል።
ሀሳብና አስተያየታቸውን ከሰጡ የግብረ ሃይሉ አባላትና ባለድርሻ አካላት መካከል በምክትል ርዕሰ-መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አበባየሁ ታደሰ፣ የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ወገኔ ብዙነህ፣ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፍሰሃ ጋረደው፣ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬን ጨምሮ የዞኖች አስተዳዳሪዎችና የፌደራል ፓሊስ ከፍተኛ የስራ ኃላፊ ይገኙበታል።
አስተያየት ሰጪዎቹ እንደተናገሩት ኮንትሮባንድና ህገ-ወጥ ንግድ በተደራጁ ህገ-ወጥ ነጋዴዎች የሚከናወንና በውስጡ ውስብስብ ወንጀሎችን ያቀፈ ተግባር በመሆኑ በተጠናከረ ቅንጅት በቁርጠኝነት መከላከል ይጠበቅብናል ብለዋል።
በስፋት በህገ-ወጥ መንገድ የሚዘዋወሩት ቤንዚንና የነዳጅ ውጤቶች መሆናቸውን የገለፁት ተሳታፊዎቹ፣ ኮንትሮባንድና ህገ-ወጥ ንግድን ለመከላከል፣ ለማዳከምና ለማጥፋት ቆርጠን መነሳት ይገባናል ሲሉ ተናግረዋል።
ኮንትሮባንድና ህገ-ወጥ ንግድ የብልጽግናን ጉዞ ለማደነቃፍ ካለው አሉታዊ ተጽዕኖ ጋር ተያይዞ ጉዳዩን ለማንም ሳንገፋ የመረጃ ደህንነትን በማዘመንና በተግባሩ ተሳትፈው በቁጥጥር ስር በሚውሉ አካላት ላይ ስር ነቀል እርምጃ በመውሰድ ኮንትሮባንድና ህገ-ወጥ ንግድን ለማዳከም እጅ ለእጅ ተያይዞ መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በኤክስፖርት ተወዳዳሪና ውጤታማ ለመሆን ምርቶች ጥራታቸውን በጠበቀ መንገድ ሊመረቱ ይገባል ያሉት ተሳታፊዎቹ፣ህገ ወጥ የግብይት ስርዓትን ለመግታት ደላሎችን ከምርት ገበያ በማጥፋት አምራችና ኤክስፖርት የሚያደርጉ አካላትን በማገናኘት ጤናማ የግብይት ስርዓት መፍጠር ያስፈልጋልም ብለዋል።
በኮንትሮባንድና ህገ ወጥ ንግድ በመከላከል በክልሉ አንዳንድ ዞኖች አበረታች ውጤቶች እያስመዘገቡ መሆኑን የገለፁት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ ኮንሶ ፣ ጌዲዮ፣ኣሪና ደቡብ ኦሞ ከተጠቀሱት ዞኖች ናቸው።
ለሀገራችን ሁለንተናዊ ዕድገት ፀር የሆነውን ኮንትሮባንድና ህገ ወጥ ንግድን ለማክሰም ሁሉም የክልላችን መዋቅሮች ራሳቸውን ሊፈትሹ እንደሚገባም በአጽንኦት ተገልጿል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ገለቦ ጎልቶሞ እንደተናገሩት ኮንትሮባንድና ህገ ወጥ ንግድ ለሁለንተናዊ ዕድገት ፀር በመሆኑ አስከፊነቱን በመረዳት የተደራጀ መረጃ ላይ በመነሳትና ህብረተሰቡን በማሳተፍ እንዲሁም አጎራባች ዞኖች በመናበብ በጋራ መግታት ይጠበቅብናል ብለዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የክልሉ ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ገብረመስቀል ጫላ በማጠቃለያ ንግግራቸው የኮንትሮባንድና ህገ ወጥ ንግድ መከላከል ተግባር በጥብቅ ዲሲፕሊን ሊመራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ኮንትሮባንድና ህገ ወጥ ንግድን በሚፈለገው ልክ ለማክሰም ግብረ ሃይሉ በተለያዩ አደረጃጀቶች ሊደገፍ ይገባል፣ከላይ እስከታች በመሰናሰል ያስፈልጋል ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገብረመስቀል ጫላ፤የፖለቲካ አመራሩም በቁርጠኝነት መምራት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል።











