የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ተቋርጦ የነበረው የካይሌ ውሃ ግንባታ ዳግም ስራ አስጀመረ።
የውሃ ስራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ከ60 ሺህ ህዝብ በላይ ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ተገልጿል።
የፕሮጀክቱ ስራ ማስጀመሪያ በአባቶች ቡራኬ የተጀመረ ሲሆን የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የኮንሶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ፍሬዘር ኮርባይዶ ናቸው።

የኮንሶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ፍሬዘር ኮርባይዶ እንደተናገሩት የካይሌ ውሃ ስራ ተጀምሮ በሥራ ተቋራጩ ከአቅም በላይ በሆነ ችግር መቋረጡን ገልፀው ህብረተሰቡ ለንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር መዳረጉን ገልጸዋል።
ኢንጂነር ፍሬዘር ጨምረው ችግሩን ለመቅረፍ የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ስራውን በአዲስ ኮንትራክተር ስራ ለማስጀመር ያደረገውን ብርቱ ርብርብ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ረዳት የመንግስት ተጠሪና የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዳዊት ገበየሁ በበኩላቸው የኮንሶ ህዝብ ለረጅም ጊዜ የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር ውስጥ መቆየቱን የገለፁት ሲሆን ክልሉ በአዲሱ አደረጃጀት ነባርና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ወደ ስራ ለማስገባት ርብርብ ማድረጉን አስታውቀዋል።
በሶስት ወር ተጠናቆ አገልግሎት እንዲሰጥ የታለመው የካይሌ ውሃ ስራ በመንግስትና በስራ ተቋራጭ ብቻ ውጤታማ መሆን ስለማይችል ማህብረሰቡ ከእነዚህ አካላት ጋር በትብብር መስራት እንደሚገባ አቶ ዳዊት አሳስበዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የዲላ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር አክሊሉ አዳኝ እንደገለፁት ውሃ መሠረታዊ የሰው ልጅ ፍላጎት በመሆኑ ከሁሉም ልማቶች ቅድሚያ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ያለ ውሃ ምንም ልማት መስራት አይቻልም ያሉት ቢሮ ኃላፊው፤ እንደ ክልል የውሃ ሽፋን ዝቅተኛ በመሆኑ አብዛኛው የክልላችን ህዝብ በንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር ውስጥ የሚገኝ መሆኑንም ጠቅሰው የክልሉ መንግስት ችግሩን ለመቅረፍ በርካታ ተግባራት እያከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል።
የኮንሶ ህዝብ በቂና ጥራት ያለው ውሃ ማግኘት አለበት ያሉት ኢንጂነር አክሊሉ፤ ከ60 ሺህ በላይ ህዝብ ተጠቃሚ የሚያደርገው የካይሌ ውሃ ስራን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ የክልሉ መንግስት ክትትል የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመዋል።
ህብረተሰቡም በበኩሉ በባለቤትነት መንፈስ ተባብሮ መረባረብ ይኖርበታል ሲሉ አሳስበዋል።
የክልሉ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ የካይሌ ውሃ ስራን ለብልሃን ባርኮን ኢንጂነሪንግ ኃ/የተ/የግ/ማህበር አስረክበው ስራው በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ የህብረተሰቡን የንፁህ መጠጥ ውሃ እጥረት ችግር እንዲቀርፍ አሳስበዋል።
መረጃው
የኮንሶ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉ/መምሪያ
ሰኔ 23/2016 ዓ/ም







