በኮንሶ የተካሄደው የእርቀ-ሰላም ጉባኤ ለዘላቂ ሠላም ፣ አንድነትና ብልፅግና ጠንካራ መሠረት መሆኑ ተገለጸ
በኮንሶ ዞን ሠገን ዙሪያ ወረዳ “ሁሉ አቀፍ እርቀ-ሰላም ኮንፈረንስ ለወረዳው ሁለንተናዊ ብልጽግና!” በሚል መሪ ቃል የተካሄደው የእርቀ-ሰላም ኮንፈረንስ ሠላምን ለማጽናት፣ የሕዝቦችን አንድነት ለማጠናከርና የልማት መሠረትን ለማጽናት ያለውን አስፈላጊነት በስፋት አንጸባርቋል።
በኮንፈረንሱ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የሠገን ዙሪያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገዛኸኝ በራቆ እንደገለጹት ያለፍንባቸውን ጊዜያት ስናስብ የተበታተነው ህዝባችን ተሰብስቦ በፍቅር ይቅር በመባባል በአንድነትና በፍቅር ኑሮአቸውን ለማስተሳሰር በመውጣታችን ቀኑን ልዩ ያደርገዋል ብለው፣ የተከሰተው ግጭት ከንብረት ውድመትና ከሰው ህይወት መጥፋት ባሻገር የማንነት ቀውስ እንዳስከተለ በማወስ ያንን ረስተን በፍቅር አሁን የሠፈነውን ሠላም ለማጽናትና የህዝቡ አንድነት እንዲጠናከር ሁሉም ሊረባረብ ይገባል ብለው
በመድረኩ የተገኙት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊና ረዳት የመንግስት ተጠሪ ኢንጂነር ፍሬዘር ኮርባይዶ፤ ቀደም ሲል በግጭት ምክንያት ባዶ የነበረው አካባቢ ዛሬ በሕዝብ መሞላቱ የተመዘገበው የሠላም ውጤት መሆኑን ገልጸው፣ የብልጽግና ፓርቲ የሚያራምደው የሕዝቦች አንድነት፣ ውይይትና ሰላማዊ አብሮነት እሴት ለዘላቂ ልማትና ብልጽግና መሠረት መሆኑን አስረድተዋል። የተገኘውን ሠላም ለማጽናትና የአካባቢውን ልማት ለማፋጠን ሁሉም የበኩሉን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባም ጠይቀዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ አቶ ዳርጌ ዳሼ በበኩላቸው፣ ሠላም በገንዘብ የማይገዛ የጋራ ሀብትና የሕይወት መሠረት መሆኑን ገልጸው፣ ሕዝቡ ከአሉባልታና ከግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶች ራሱን በመጠበቅ በይቅርታ፣ በእርቅና በአንድነት የሠላም መልዕክተኛ እንዲሆን አሳስበዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፍሰሃ ጋርደው ደግሞ፣ ሠላም ከሁሉም የላቀ የፈጣሪ ስጦታ መሆኑን ጠቅሰው፣ ሠላም ሲኖር ልማት፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ እድገት እንደሚረጋገጥ፣ ሠላም ሲጠፋ ደግሞ ሁሉም እንደሚጎዳ አስገንዝበዋል። ሕዝቡም አንድነቱን በማጠናከር ፀረ-ሠላም ኃይሎችን በማጋለጥ ለህግ እንዲያቀርብ ጥሪ አቅርበዋል።
በዚሁ ወቅት የኮንሶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገለቦ ጎልቶሞ፣ የኮንሶ ሕዝብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚታወቅባቸው ዕንቁ ባህላዊ እሴቶች መካከል ባህላዊ የእርቅ ሥነ-ሥርዓቱ አንዱ መሆኑን በመግለጽ፣ ይህን የአባቶች የሠላምና የይቅርታ ባህል በማጠናከር ዘላቂ ሠላምና ብልጽግናን ማረጋገጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።













በመድረኩ ጥላቻ ፣አለመግባባት ክፉና ትውልድ የሚቀጭ መሆኑን የሚያንጸባርቁ መልዕክት አዘል ባህላዊና ጨዋታዎችና ስፖርታዊ ትርዒቶች የቀረቡ ስሆን፣ በመጨረሻም በአካባቢው ሠላም እንዲሰፍን የላቀ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ግለሰቦችና ተቋማት የእውቅና ሽልማትና የምስጋና ምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።






