



የኮንሶ፣ የኧሌ እና የጋርዱላ ዞኖች የፊት አመራሮች እና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች የጋራ ሠላምና አንድነት በሚጠበቅባቸው ጉዳዮች ላይ በኮንሶ ዞን ካራት ከተማ የሶስትዮሽ የምክክር መድረክ አካሂደዋል፣
በምክክሩ ላይ የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር-ቤት ዋና አፈ-ጉባዔ የተከበሩ አቶ አዳማ ትንጳዬ ህዝባችን ከተቀናጀ በጣም ከፍተኛ ውጤት ማምጣት የሚችል ህዝብ ነው ሲሉ ገልጸው፤ ለዚህም ለጋራ ለውጥ የሚሆንን ብልሃት በመፍጠር፣ እንደዚሁም እንደ ምሁርና እንደ አመራር ከመቼውም ጊዜ በላይ ቆርጦ በመነሳት ለህዝብ አንድነት መስራት ይጠበቅብናል፤ የተለያዩ ኮሚቴዎችን በማቋቋምም የተጠናከረ ስራ መስራት ይገባናል ብለዋል።
የተከበሩ አቶ አዳማ ትንጳዬ እና የክልሉ ረዳት የመንግስት ተጠሪና የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ኢንጂነር ፍሬዘር ኮርባይዶ በጋራ ባደረጉት ንግግር የሦስቱን ዞኖች ህዝቦች በማቀራረብና ዘላቂ ጉርብትናን በማጠናከር፣ ብሎም አመራሩ ወጥ የሆነ አስተሳሰብ በመያዝ የህዝቡን አንድነት እና የቀድሞ ቤተሰባዊነት ማደስ ይጠበቅበታል ብለዋል።
ኢንጂነር ፍሬዘር ኮርባይዶ በበኩላቸው የየመዋቅሩ አመራሮች እና ምሁራን ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎች ያካተተ ተከታታይ ውይይቶችን በማካሄድና ሀገር በቀል ባህላዊ የግጭት አፈታት ዜደዎችን በመጠቀም ህዝባዊ ትስስሮችን ለልማት መጠቀም ይኖርባቸዋል ብለዋል።
የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችን፣ ስፖርታዊ ውድድሮችን እና የባህል ልውውጦችን እንደዚሁም ህዝብን የሚያሰባስቡና የሚያስተሳስሩ ኩነቶችን በመፍጠር በትውልድ ውስጥ አንድነትን ለማስረጽ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል ኢንጂነር ፍሬዘር።
አስተያየት ሰጪ የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የኮንሶ፣የኧሌ እና የጋርዱላ ህዝቦች በመዋቅር አደረጃጀት ልዩነት እንጂ በትውልድ የዘር ግንዳችን ከአንድ ቤተሰብ ነው ሲሉ ተናግረው፤ በመሆኑም በእነዚህ ቤተሰቦች መካከል የነበረውን አንድነትን ማሳደስ ያስፈልጋል በማለት ተናግረዋል።
በቀጠናዎቹ በተደጋጋሚ የሚከሰቱ የግጭት አዙሪቶች የቀጠናዎቹን ስም አጠልሽተዋል ያሉት ተሳታፊዎቹ፤ የተዛቡ ትክርክቶችን በማረምና እንደ አመራር የጋራ አንድነትን በማጠናከር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችን በየደረጃው በተደራጀ መንገድ ማስቀጠል ያስፈልጋል ብለዋል።
አንዳችን ከአንዳችን ተለይተን የትም አንደርስም፤ ስለዚህ ወደ ቀድሞ አንድነታችን ልንመለስ ይገባል ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ፤ በአሉባልታ ሳይሆን የፊት ለፊት ውይይቶችን በማድረግ፣ የሶስቱን መዋቅሮች የኃይማኖትና የባህል አባቶች ብሎም የጎሳ መሪዎችን በማቀናጀት
በልዩነት ውስጥ ያለውን አንድነት ማጠናከር ለዚህም ልዩ ትኩረት ሰጥተን በጋራ መረባረብ ይጠበቅብናል ሲሉ ገልጸዋል።
በስተመጨረሻም የተከበሩ አቶ አዳማ በየጊዜው የሚከሰቱ አለመግባባቶች የሚያስከትሉት ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ቀውሶች በቀላሉ የሚታዩ አይደለም ያሉ ሲሆን፤እኛ የሶስቱ መዋቅሮች አመራሮችና አስተባባሪዎች ተቀናጅተን በማህበረሰቡ ውስጥ ለውጥ ማምጣት ይጠበቅብናል ሲሉ ገልጸዋል።
መንግስትን ለማዳከም የሚንቀሳቀሱ አካላትን ለመመከት አንድነታችንን ማጠናከር ይጠበቅብናል ያሉት የተከበሩ አቶ አዳማ፤ የሶስትዮሽ የጋራ ፕሮጀክትን በማቋቋም ውጤታማ ስራን መስራትና ሌት ተቀን ሳንል በሶስቱም መዋቅሮች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ስራዎችን ማጠናከር ይገባናል፤ ችግሮችን ወደ ዕድል ለመቀየርም ሳንሸማቀቅ አበክረን መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
መረጃው
የኮንሶ ዞን መንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት
መጋቢት 02/2018 ዓ.ም







